የመስክ ጉብኝት ተካሄደ

በተለያዩ የሰብል ዝርያዎች ላይ የተሰሩ የምርምር ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ያለመ የመስክ ጉብኝት ተካሄደ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ ምሁራን በአኩሪ አተር፣ በአቮካዶና ቀይ ሽንኩርት ሰብሎች ላይ በሲዳማ ክልል ባሉ ወረዳዎች ያሉ
አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰሩ የምርምር ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመመልከት ያለመ የመስክ ጉብኝት ዛሬ በአለታ ወንዶና ሸበዲኖ ወረዳዎች ተካሂዷል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በመስክ ምልከታው ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በዩኒቨርሲቲ ምርምር አካሄጅነት፣ በGIZ የገንዘብ ድጋፍ እና በክልልና ወረዳዎች ግብርና ቢሮዎች የሶስችዮሽ ትብብር በአኩሪ አተር፣ አቮካዶ እና ቀይ ሽንኩርት ሰብሎች ላይ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ በምርምር የተለዩ ሰብሎችን የማስተዋወቅና ለአርሶአደሩ ተደራሽ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በሲዳማ ክልል ባሉ አራት ወረዳዎች ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚደንቱ በአሁኑ ወቅት በሁለት ወረዳዎች ማለትም በአለታ ወንዶና ሸበዲኖ ወረዳዎች በሚገኙ የአርሶ አደር ማህበራት ላይ የመስክ ምልከታው እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው መንግስት አርሶአደሩ እራሱን በምግብ ከመቻል አልፎ ገቢ በሚያመነጩና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በሚያሳድጉ የሰብል ዝርያዎች ላይ ማተኮር እንዲችሉ ለማድረግ በምርምር የተገኙ አዳዲስ ዝርያዎችን ማስተዋወቅ ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ከዩኒቨርሲቲው ጋር በሚሰሩ የጋራ ተግባራት አርሶአደሩ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እንዲላመድ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ዳይሬክተሩ በታየው ውጤታማ ምርታማነት የተነሳ በርካታ አርሶአደሮች የሰብል ዝርያዎቹን መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በግብርና ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ በፕሮጀክቱ ሶስት ዋና ዋና ተግባራት እንደሚከወኑ ይኸውም ካሉ ዝርያዎች መካከል ለአካባቢው ተስማሚ የሆነውን ዝርያ መምረጥ፣ ቀጥሎም የተመረጠውን ዝርያ መሞከርና ምርታማነቱን ማየት፣ እና በመጨረሻም ምርታማ የሆነውን ዝርያ በይበልጥ ማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል። ዶ/ር ባዩ ጨምረውም በተካሄደው የመስክ ምልከታ ፕሮግራም ላይ በአኩሪ አተር ላይ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ገልጸው ይህንኑ ስኬት በአቮካዶና ቀይ ሽንኩርት ላይ ለመድገም የጋራ ቅንጅታዊ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በግብርና ኮሌጅ የአግሮኖሚክስ መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ቴዎድሮስ አያሌው ደግሞ በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ አሳሳቢ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥና የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ዋነኞቹ ስለሆኑ በአንድ በኩል የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል በሌላ በኩል ደግሞ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የአስተራረስ ስነ-ዘዴና የሰብል ዝርያ አይነትን መምረጥ ግድ የሚል መሆኑን ገልጸው እንደ አኩሪአተር ያሉ ሰብሎች በዚሁ ዘርፍ እንደሚመደቡ አብራርተዋል።

በሁለቱ ወረዳዎች ከተካሄደው የመስክ ምልከታ በኋላ በግብርና ኮሌጅ በባዮ ፈርቲላይዘር ላይ የተሰራውን ስራ አስመልክቶ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ይኸው ቴክኖሎጂው ለኬሚካል ማዳበሪያ ግዢ የሚወጣውን ወጪ በመቀነስም ሆነ የተሻለ ምርት እንዲገኝ የሚያበረክተው ሚና ትልቅ ስለመሆኑ ተገልጿል።

Contact Us

Office of External Relations & Communications 
Phone:  +251 46 220 5168
International Relations
Public Relations 

Touch Us

Registrar Contact 

Registrar Directorate 
Phone: 0462200229
Email: registrar@hu.edu.et